መግቢያ

የቀርከሀ ውጤትን በባህላዊ ዘዴ ማምረትና መጠቀም በአለም ዙሪያ በሚገኙ አዳጊ ሀገሮች የተለመደ ጉዳይ ነው።ቀርከሀ ካለው ውብ አቋም፣ ቀላል ክብደት፣ የተፈጥሮ ጥንካሬና አነስተኛ ዋጋ ሳቢያ ቀርከሀ በአፍሪካ ሀገሮች የቤት እቃ ለሚያመርቱ ባለሙያዎችና ነጋዴዎች በአነስተኛ ወጪ ወደ ስራ የሚያስገባ ተመራጭ የስራ መስክና የገቢ ምንጭ አማራጭ ሆኖ  እያገለገለ ይገኛል። ይህ ሙያዊ ፅሁፍ የቤት አቃዎችን ከድፍን ቀርከሀ የማምረትን ዘዴ ደረጃ በደረጃ የሚያሳይ ነው። በዚህ ፅሁፍ ውስጥ የተገለፁት የአሰራር ዘዴዎች ወይም ሙያወች በተለያዩ የቀርከሀ ዝርያወች ሊተገበሩ የሚችሉ ሲሆን በተለይም ለመካከለኛና ክፍተኛ መጠን ማለትም ከ 3 እስከ 30 ሴንቲ ሜትር ዲያሜትር ለሚደርስ ዙሪያና ከአንድ ሴንቲ ሜትር በላይ የግርግዳ ውፍረት ላላቸው የቀረከሀ ዝርያወች የበለጠ ተስማሚ ይሆናል።

የቀርከሀ የቤት እቃ ስራ አሰራር አጭር መግለጫ

1.ጥሬ ዕቃ

2.ማከምና መንከባከብ

3.ማቃናትና ማጉበጥ

4.ንዑስ ክፍሎች ዝግጅት

5.መላግና ቅርፍት መፋቅ

6.መለካት

7.ጫፎችን መሙላት

8.ቅርጽ ማውጣት

9.መገጣጠም

10.ስንጥቅና ክፍተትን መሙላት

11.ማጽዳትና ማለስለስ

12.መቀባት

13.ማሸግና

14.በአግባብ ማስቀመጥ

ለስራ የደረሰ ቀርከሃ አመራረጥ

ለቀርከሃ ቁሳቁስ ወይም የቤት እቃ ስራ የሚውል ቀርከሃ የበሰለ ማለትም በእድሜ ከ 3 አመት ያላነሰ በማድረግ ሊከሰት የሚችለውን በነቀዝና ፈንገስ  የመጠቃት አደጋ መቀነስ ይቻላል። ለቤት አቃዎች ስራ የሚውል ቊርከሃ ዝርያ ከዲዘይኑና ከሚፈለገው ጥንካሬ  ጋር መጣጣም ይኖርበታል። የተሰነጠቀ ወይም የተጎዳና  በነቀዝና በፈንገስ የተጠቃ ቀርከሀ መወገድ ይኖርበታል።

ቀርከሃን ማከምና መንከባከብ

ቀርከሃን ማከምና መንከባከብ የቀርከሃ ውጤትን የአገልግሎት ዘመን በከፍተኛ ደረጃ የተሻለ ያደርገዋል። ለተጨማሪ ግንዛቤ እባክዎ “Preservation and Treatment” የሚለውን ጥናታዊ ፅሁፍ ይመልከቱ።

ቀርከሃን ማጉበጥና ማቃናት

መገጣጠሚያው የተስተካከለ በቀላሉ የሚገጠምና ጥራት ያለው  ውጤት ለማግኘት ለቤት እቃዎች ስራ የሚውል የቀርክሃ ዘንግ የተቃና ቀጥታው የተጠበቀ መሆን ይኖርበታል። ይህን ለማድረግ በዲዛይኑ መሰረት ከሚፈለገው ትክክለኛ መጠን በላይ ከ 1 ሜትር ባላነሰ አስረዝሞ መቁረጥ።ለምሰሌ የሚፈለገው ትክክለኛ መጠን 7 ሜትር ከሆነ 8 ሜትር ቀርከሀ ለክቶ መቁረጥ::

የቀርከሀ ማቃኛ አሰራር

ማንኛውንም የእንጨት አይነት ከ 200 እስከ 250 ሴንቲ ሜትር እስከ 30 ሴንቲ ሜትር ዲያሜትር  ውፍረት   ወይም ስፋት ያለው ያገለግላል ።ይሁን እንጂ የቀርከሀውን ቁመትና ውፍረት ማገናዘብ ተገቢ ነው፡፡ በእንጨቱ ላይ ቀርከሀውን በደንብ አስገብቶ ለማንቀሳቀስ በሚያስችል መልክ ቀዳዳ ማውጣት። ከዚህ በኋላ እንዳይንቀሳቀስ አድርጎ ማቃኛውን መትከል፤የማቃኛው ከፍታ የባለሙያዎችን የቁመት መጠን ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርበታል።የጎበጠውንና መቃናት የሚፈልገውን ክፍልና አካባቢውን በእሳት ሀይል ማሞቅ። በእሳት በሚሞቅበት ጊዜ የመለብለቢያ መሳሪያውን ወደፊትና ወደኋላ ሳይፈጥኑና ሳይዘገዩ በማንቀሳቀስ ሊፈጠር የሚችለውን በተወሰነ ክፍል ብቻ መጥቆርና ብሎም መቃጠል መቆጣጠር ያስፈልጋል። የቀርክሃን  ዘንግ ለማሞቅ የሲሊንደር ጋዝና ኩራዝ ወይም ቶርች መጠቀም ወይም ደግሞ በባህላዊ አሰራር ከሰልና እንጨት ወይም የባከነ ቀርከሃን ስራ ላይ ማዋል ይቻላል። ቀርከሃ በሚሞቅበት ጊዜ ስለሚላላና የመለጠጥ በህሪው ስለሚጨምር ሙቅቱንና ግፊትን በማመጣጠንና በመጫን ማጉበጥ ወይም ማቃናት።

የቀርከሀን ዘንግ ማጉበጥ ∕ ማቃናት

ቀርከሀን ለማጉበጥ ማንኛውንም አይነት ጠፍጣፋ እንጨት ወይም ግንድ መርጦ ማዘጋጀትና ለማቃኛነት መጠቀም  ቻላል። በተመረጠው የማቃኛ  እንጨት ላይ የሚጎብጠውን ወይም የሚቃናውን ቀርከሀ ሙሉ ለሙሉ ማስገባት የሚያስችል ቀዳዳ መብሳት ∕ ማውጣት። ቀርከሀውን በቀዳዳው ውስጥ በማስገባት የሚጎብጠውን ክፍልና እካባቢውን በእሳት በመለብለብና በማሞቅ ወደሚፈለገው አቅጣጫ በመጫን ማረቅ። የሙቀቱና የግፊቱ መጠን ካልተመጣጠነ ቀርከሀው ሊሰነጠቅ ወይም  ሊቃጠል ስለሚችል ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል። የተፈለገው ውጤት መገኘቱ ሲረጋገጥ ውሀ የተነከረ ጨርቅን ወይም ስፖንጂን በመጠቀም የሞቀውን ክፍል ማቀዝቀዝና አዲሱን ቅርጽ ይዞ እንዲቀጥል ማስቻል። ይህን ሂደት በተደጋጋሚ በማከናወንና በአንድ አይን በማይት ሙሉ ለሙሉ ቀጥታ መሆኑን ማረጋገጥ ወይም በዲዛይኑ መሰረት መጉበጡን∕ ተፈላጊውን ቅርጽ መያዙን ደግሞና ደጋግሞ በአናጺ እይታ በመመልከት ማረጋገጥ::

የፕሮጀክት ስራ ንኡስ ክፍልች ዝግጅት

የፕሮጀክቱን ዲዛይን መሰረት በማድረግ ክፍሎቹን ለይቶ መረዳትና መዘርዘር፣ የእያንዳንዱን ክፍልና ንኡስ ክፍል ትክክለኛ መጠን መለካትና በዝርዝሩ መሰረት ክፍሎቹን ማዘጋጀት።የቀርከሀን የታችኛውን ክፍል በዋናነት ዲዛይኑን መሰረት በማድረግና የዙሪያ ልኬቱን፣ የስጋ መጠኑና ጥንካሬውን ግምት ውስጥ በማስገባት ለቋሚ መጠቀም የሚመከር ሲሆን ቀሪውን ክፍል እንደአስፈላጊነቱ ለማፈኛ፣ ለወለል ለመወጠሪያና ለመሳሰሉት መጠቀም። ይህ ዘዴ ቀርከሀን በየደረጃው መጠቀም ከማስቻሉ በላይ ብክነትን ለመቆጣጠር ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል።የንኡስ ክፍሎች ልክ ተገነዝቦ የተመረጠውን ቀርከሀ በሜትር በመለካት በእርሳስ መሰል መጻፊያ ምልክት ማድርግ።

ማስታወሻ:-ለስራ የሚመረጠው ቀርከሀ ዴዛይኑን መሰረት ያደረገ መሆን ይገባዋል።ይህ ማለት የቀርከሀው ውፍረት፣ የግርግዳው መጠን፣ ውጫዊ ገጽታውን ያካተተ ይሆናል።የተሰነጠቀ፣ የተቀጠቀጠና ማንኛውም አይነት ጉዳት ያለበት ቀርከሀ መወገድ ይኖርበታል።

የቀርከሀ ስራ መሰረተዊ ተግባሮች/ ቅርፍት መፋቅ 

ቀርከሀ አንጓው ላይ ከሌላው ክፍሉ ጋር በማነጻጸር ሲታይ ከፍ የማለት ባህሪ አለው። ይህንን ለማስወገድ አንጓውን በአንጓ መላጊያ፣ በሶስት ማእዘን ሞረድ ወይም በአንግል ግራይንደር ማስተካከል የመጀመሪያ ስራ ይሆናል። በመቀጠል የቅርፊት መፋቂያን በመጠቀም ከላይ ወደ ታች በመፋቅ ቅርፍቱን ብቻ ማስወገድ። በሚፋቅበት ጊዜ የቀርከሀው ጠንካራውና የላይኛው ክፍል እንዳይነካ መቆጣጠር ተገቢ ሲሆን ይህ ድርጊት በሰው ሀይል ቢሰራ ይመረጣል።

የመጋጠሚያ ዝግጅት

ለመለካት በቅድሚያ የቀርከሀ ማስመሪያ ወይም መለኪያ ማዘጋጀት ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው። የቀርከሀ ማስመሪያው አያንዳንዱን ክፍል ለመስፈር፣ የማጠፊያ ቦታውን ለመለየትና ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ በተለያየ አቅጣጫ በመለካት ለማስተካከል በሚያስችል መልኩ በሜትር ተለክቶና ይዘጋጃል። በመቀጠል ማስመሪያውን በመጠቀም  ለመለያ ወይም ለማነጻጸሪያ ቀጥታ መስመር በቀርከሀው ላይ ማስፈር። መስመሩን መሰረት በማድረግ ምልክቶቹን ከመለኪያው ወደ ፕሮጀክቱ ማሽጋገር ጥርጣሬ ሲፈጠር ሜትርን ተጠቅሞ ማረጋገጥ ሊፈጠር የሚችልን ስህተት ለማረም ይረዳል።  ምልክቶችን በአግባብና ማስቀመጥ ለማጠፊያው ለስኩ መስተካከል የተፈለገውን ቅርጽ ለማስያዝና ለምርታማነት ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል።

ክፍተትን መሙላት

ቀርከሀ በተፈጥሮ አንጓዎቹ ክፍት ናቸው። ስለሆነም አገጣጠሙን የጠነከረ ለማድረግ በቅድሚያ ክፍተቱን መሙላተ የግድ ይሆናል።ለዚህም እንጨት ወይም ስንጥቅ ቀርከሀን በማስተካከል መጠቀም ይቻላል።

ቅርጽ ማውጣትና መግጠም

በተገቢው መንገድ 45 ዲግሪ በመለካትና ከቀርከሀው ዙርያ በከፊል በመጋዝ በመቁረጥ፣ በመሮና መዶሻ የተፈለገውን ቅርጽ ማውጣት።

ልዩ ማስታወሻ:-መገጣጠሚያው በቀርከሀው ክፍት ክፍል ላይ በሚውልበት ጊዜ ሁለቱንም ክፍት ጫፎች ሞልቶ ከሁለቱም ጫፍ በመነሳትና በግራና በቀኝ 45 ዲግሪ በመቁረጥና ምላስ በማውጣት ትክክለኛ መገጣጠሚያ መስራት ይቻላል።

ምላስ አወጣጥ

በተለካውና መሰረት መዶሻና ጠፍጣፋ መሮ በመጠቀም 45 ዲግሪ ጠብቆ በመቁረጥና ምላስ በማውጣት በትክክል እንዲገጠም ማዘጋጀት በመቀጠልም የተዘጋጀውን ምላስ ልክ በዋናው ፕሮጀክት ላይ መለካት። በመግጠም ጊዜ ሊፈጠር የሚችለውን ችግር ከወዲሁ ለመከላከል ኮድ ወይም ምልክት መስጠት። በመጀመሪያ በመጋዝ በመቁረጥና  ቀጥሎም መዶሻ፣ ጠፍጣፋ መሮና ሞረድን በመጠቀም በተለካው መሰረት ቀዳዳውን ማውጣት ።የቀዳዳው ጥልቀት መጠን ከቀርከሀው ዲያሜትር ከፍ ያለ ቢሆን ይመረጣል።ቀዳዳውን በምላሱ ትክክል ወይም እኩል ማውጣት የተሻለ እንዲሆን ይረዳል።

 ዲግሪ ማእዘን አገጣጠም

ለማእዘን አገጣጠም ተመጣጣኝ መጠን ያላው ቀርከሀ  አንጓ ጠብቆ መቁረጥ ወይም ክፍት የሆነውን የቀርከሀ ክፍል ከላይ በተዘረዘረው መንገድ መሙላት። በመቀጠል በሁለቱም ጫፍ በኩል በ45 ዲግሪ በመቁረጥ በትክክል ማጋጠም።

በክብ ቀዳዳ መግጠም

ክብ ቀዳዳ በኤሌክትሪክ መሰርሰሪያ ወይም ክብ መሮና መዶሻን በመጠቀም ማውጣት ይቻላል። በመቀጠል በቀዳዳው የሚገባውን ቀርከሀ በማስተካከል በትክክል እንዲገጥም በማድረግ መሰካት።

ማስታወሻ:- የማእዘን ወይም ማንኛውም አይነት አገጣጠም ትክክለኛ ቦታውንና ዲዛይኑን የተከተለ መሆን ይኖርበታል::

አገጣጠም

በቅድሚያ የተዘጋጀውን የፕሮጀክት ክፍል ለመግጠም ከዚህ ቀጥሎ በተዘረዘረው መሰረት ደረጃ በደረጃ ማከናወን ይቻላል፣

ደረጃ 1.  የተዘጋጁትን የቀርከሀ ክፍሎች ማሰባሰብ

ደረጃ 2.  ኮላ ወይም ሌላ ማጣበቂያ መቀባት

ደረጃ 3.  በገመድ ማሰርና በትክክል መገጣጠሙን በመለካት ማረጋገጥ

ደረጃ 4.  በመጨረሻም የቀርከሀ ሚስማር በመምታት ማጠናከር

ክፍሎቹ በኮላ ከተያያዙና ከተጣበቁ በኋላ በገመድ ወይም ማሰር ወይም በቀርከሃ ሚስማር ማጠናከር። የፐሮጀክቱን እርዝመትና ጎን እንዲሁም ከአንዱ ማእዘን ወደ ተቃራኒው መእዘን ያለውን ርቀት በመለካት ሁለቱ ክፍሎች እኩል መሆናቸውን ማረጋገጥ። የማስተካከሉ ስራ ኮላው ወይም ማጣበቂያው ከመድረቁ በፊት መከናወን ይኖርበታል በገመድ እንደታሰረ ወይም ኮላው ከደረቀ በኋላ በኤሌክትሪክ ወይም በእጅ መሰርሰሪያ የሚስማር ቀዳዳ መብሳት። ሚስማሩን በተበሳው ቀዳዳ ውስጥ በማስገባት በመዶሻ መምታት ። የሚሰማሩ መጠን ከቀዳዳው ስፋት በ 1 ሚሊሜትር የሚበልጥ ሆኖ መዘጋጀት ይኖርበታል።

ማስታወሻ:-ማሸግና በተለያዩ አቅጣጫዎች በመለካት ማስተካከልና ማረጋገጥ ያለ ጊዜ ክፈተት መከናወን የሚገባው ሲሆን ውሀ ልኩ በተጠበቀ ወለል ላይ መከናወን ይኖርበታል።

አገጣጠም

የቀርከሀ ሚስማር አዘገጃጀ

የቀርከሀ ሚስማር በተለያየ መጠን ይዘጋጃል። አዘገጃጀቱም ቀርከሀውን በቅድሚያ በ4 ማእዘን በመሰንጠቅ ይጀመራል።ከላይ ታች በቢላዋ በመጥረብ ታችኛውን ክፍል እንዲሾል ማድረግ። የሚዘጋጀው ቀርከሀ ሚስማር ከቀዳዳው ከ1 ሚሊሜትር ባላነሰ ከፍ ማለት ይኖርበታል።

የርብራብ ዝግጅት

የሚሰራውን ፕሮጀክት መሰረት አድርጎ የሚፈለገውን የርብራብ ወይም ስንጣቂ መጠን መለካትና ቀርከሀ መቁረጥ። ከትክክለኛው የስንጣቂ መጠን 1 ሚሊሜትረ ጨምሮ መሰንጠቅ፣ የስንጣቂዎቹን ግራና ቀኝ በማስተካከል እኩል አድርጎ ማዘጋጀት። ለርብራብ ከ1. እስከ 2. ሴንቲሜትር የሚመረጥ የስፋት መጠን ነው።

የርብራብ አገጣጠም

ርብራብ የሚገጠመው በመዋቅሩ ላይ በመሆኑ በቅድሚያ መዋቅሩ መጠናቀቅ ይኖርበታል።የተዘጋጀውን ርብራብ በመዋቅሩ ላይ በዲዛይኑ መሰረት ክፍተቱን ጠብቆ የተዘጋጀን ፎርም በመጠቀም ማስቀመጥ። በእጅ ወይም በኤሌትሪክ መሰርሰሪያ ቀዳዳ በማውጣት በሚስማርና በኮላ ማያያዝ። ቀርከሀን በሚስማር ከማያያዝ ከመሞከር በፊት በስንጣቂው ላይ ቀዳዳ ማውጣት መሰንጠቅን ያስወግዳል።

በቅደም ተከተል ማከናወን

ክፍተትን መዝጋት∕ ማረምክፍተትን መዝጋት∕

የተፈጠረ ክፍተት ካለ ወይም ስንጥቅ ካጋጠመ የመጋዝ ብናኝና ኮላ በማዋሀድ ቀዳዳዎቹን መሙላት። ውህዱ በጣም ቀጭን ወይም ወፍራም እንዳይሆን መጠንቀቅ ያስፈልጋል።ስንጥቅና ክፍተቱ ከተሞላ በኋላ ወዲያውኑ በእርጥብ ጨርቅ ማጽዳት:: በቀርከሀ ስራ የማይፈለጉ ስንጥቆች የተለመዱ ናቸው በመሆኑም መሙላት ወይም ማረም ተገቢ ነው። ስንጥቅን ለመሙላት የመጋዝ ብናኝ ያገለግላል። የመጋዝ ብናኝን መሰብሰብና ደቃቁን ክፍል ብቻ መለየት። የተለየውን ብናኝ በቀጭን ኮላ መለወስና ስንጥቁን መሙላት። አያይዞም ትርፍራፊውን ወዲያውኑ በማጽዳት ከ 2 እስከ 3 ሰአት ለሚሆን ጊዜ እንዲደርቅ መተው።

ማጽዳትና ማለስለስ

ማንኛውም አላስፈላጊ ነገር ከፕሮጀክቱ ላይ መነሳት ይኖርበታል፣ በተለያየ ሁኔታ የተፈጠረ ሽክርትም መለስለስ ይኖርበታል።ጠፍጣፋና ግማሽ ክብ መሮን በመጠቀም የኮላ ጠብታ፣ ትርፍ የሚስማር ጫፍ፣የመሳሰሉትን መፋቅና ማስወገድ በመቀጠልም ደረጃ በደረጃ ማለስለስ። በመጀመሪያ ደረጃ 80 ቁጥር በመቀጠልም 120 ቁጥር የብርጭቆ ወረቀት በመጠቀም ማለስለስ። ለከፍተኛ ደረጃ ልስላሴ 220 ቁጥር የብርጭቆ ወረቀት መጠቀም ይቻላል። የቀርከሀን ውጤት ስራው እንደተጠናቅቅ አለበለዚያም ለመጒጒዝ በሚፈለግበት ጊዜ ማሸግ ይቻላል። በጋዜጣ፣ በስታይሮፎም∕ ማሸጊያ∕፣ በጠንካራ ወረቀትና በጆኒያ በመጠቅለል በገመድ ማሰር ያስፈልጋል።የቀርከሀን ውጤት ስራው እንደተጠናቅቅ አለበለዚያም ለመጓጓዝ በሚፈለግበት ጊዜ ማሸግ ይቻላል። በጋዜጣ፣ በስታይሮፎም∕ ማሸጊያ∕፣ በጠንካራ ወረቀትና በጆኒያ በመጠቅለል በገመድ ማሰር ያስፈልጋል።

መቀባትና ማጠናቀቅ

በደንብ ከጸዳና ከለሰለሰ በኋላ ሁለት ዙር መቀባት። ለመቀባትም አንድ ኪሎ ቫርኒሽ በ100 ሚሊሊትር ቲነር ወይም ጋዝ መበጥበጥ።በሚቀባበት ጊዜ በንጹህ አካባቢ ከ 6 እስከ 8 ለሚሆን ሰአት በማቆየት ማድረቅ። በደንብ ሲደርቅ ከመጀመርያው በጥቂቱ ቀጠን ያለ ማለትም 1 ሊትር ቫረኒሽ ከ 200 እስከ 250 ሚሊ ሊትር በሚደርስ ቲነር በመበጥበጥ በድጋሚ መቀባትና ከ 6 እስከ 8 ሰአት ለሚሆን ጊዜ ማድረቅ።

ማስገንዘቢያ

1.ቫርኒሽ ሲቀባ ከግራ ወደ ቀኝ ወይም ከላይ ወደ ታች ገሬይን ወይም ጭረቱን አቅጣጫ ተከትሎ መሆን ይገባዋል።

2.በሚቀባበት ጊዜ እጅን እኩል ማድረግ፣ ከሚፋለገው በላይ ቫርኒሽ አለመጠቀም፣ በአየር ምክኒያት የቫርኒሽ እምባ ወይም እንዳይፈጠር መቆጣጠር።

3.ክቆሻሻና አቧራ ነጸ በሆነ ቦታ መቀባትና ቢያንስ ለ 8 ሰአታት ያህል ማድረቅ።

Pin It on Pinterest

Share This