የመኝታክፍል በመኖሪያ ቤት ውስጥ ትልቁን የማገልገል ሚና ይጫወታል፡፡ የሰውልጅ የእድሜውን አንድ ሶስተኛ በመኝታክፍል በተለይም በአልጋው ላይ ያሳልፋል፡፡ መኝታ ሳይታሰብበት የሚደረግ ነገር ቢሆንም ከሌሎች የኑሮ አሰራሮች ባልተናነሰ አሰፈላጊ ነው፡፡ ጥሩ እንቅልፍ ማግኘት ጤናማ የዕድገት ሂደት እንዲኖር ያደርጋል፡፡ ልጆች በመኝታ ቤታቸው ውሰጥ መተኛት፣መጫወት፣ራስን ማስተካከል እና የመሳሰሉትን ለአካላዊም ሆነ አእምሯዊ እድገት አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ያከናውናሉ፡፡ በቤት ውስጥ ቢያንስ አንድ ስፋት ያለው ክፍል ውስጥ ለማንቀሳቀስ የሚቻሉ የቤት-ዕቃዎችን በማስገባት ልጆች በቤት ውስጥ አጠቃላይ አንቀሳቃሽ የሆኑ አነቃቂ ጨዋታዎችን እንዲጫወቱ ማመቻቸት ያስፈልጋል፡፡

ለልጆች የመኝታ-ቤት አካባቢን ለማበልፀግ መታየት ያለባቸው ፅንሰ ሃሳቦች

የልጆች የእንቅስቃሴ አካባቢ በአላማ ዕቅድ እና ፍልስፍና የሚለዋወጥ ቢሆንም ለሁሉም አካባቢ መተግበር የሚችሉ ልኬቶች አሉ፡፡እነዚህም

 1. ልስላሴ፦ ለስላሳና ፈጣን ምላሽ የሚሰጥ አካላዊ አካባቢ ለልጆች ተደራሽነት አለው፡፡ ልጆች ደህንነታቸው እንደተጠበቀ እንዲሰማቸውና አቅማቸውን መልሰው እንዲያድሱ ያግዛል፡፡
 2. መረጋጋት፦ የመረጋጋት ጉዳዮች የተወሳሰቡና በአንድ የተወሰነ መሳሪያ መገኘት ወይም አለመገኘት ጉዳዮች አይደሉም፡፡ የምንጠቀማቸው እቃዎች በአንድ እይታ ውስጥ የተፈለገውን ያህል ሊሰሩ፤ በሌላው እይታ ደግሞ የማያስተማምኑ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በመሆኑም በመጠቀም ውስጥ ተለዋዋጭነት ያላቸው የቤት-ዕቃዎችን መምረጥ የተሻለ ይሆናል፡፡
 3. ደህንነት፦ ደህንነት የወላጆች እና የልጆች ግምትና የእቃውን አጠቃቀምና አገባብ የሚያማክለው ቢሆንም ለአደጋ የሚሰጥ የተለመደው ምላሽ ያልተመቸን የቤት-ዕቃ ማስወገድ ነው፡፡ የአውሮፓ የደረጃዎች ኮሚቴ ደህንነትን ጉዳትን ማድረስ ወይም መጎዳት እና መገኘት ያለበት ግልጋሎትን ማጣት ብሎ ፍቺ ይሰጠዋል፡፡ ጉዳትን ለመቀነስ፤ ለእነዚህ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል፡፡
 4. የልጁ የእድገት ደረጃ (ችሎታ፣ክብደት፣እድሜ ወዘተ)
 5. ልጁም ሆነ እቃው ንክኪ በሚያደርጉባቸው አካባቢዎች ያለው አደጋ
 6. ትክክለኛ ወይም ለወደፊት የሚገኝ ጥቅም (ትክክለኛ አጠቃቀም እንደ ልጆች የጥንቃቄ ደረጃ እንጂ እንደ አዋቂዎች አማካይ ደረጃ የሌለው መሆኑን ታሳቢ በማድረግ)
 7. የልጅነት ጊዜ ጉዳት እና የጉርምስና ጊዜ ጉዳቶች በብዙ አገራት የሞት እና የአካል ጉዳት መንስኤ በመሆናቸው የህፃናት ደህንነት የማህበረሰብ ትልቁ ዓላማ መሆን አለበት፡፡
 8. ግላዊነት፦ በአንድ መኖሪያ ስፍራ ውስጥ የግላዊነት ደረጃዎች መኖራቸውን ማወቅና አምኖ መቀበል ያስፈልጋል፡፡ ልጆች እና አዋቂዎች በቤት ውስጥ የመንቀሳቀሻ ስፍራ ሊኖራቸው ይገባል፡፡

ጥናቶች እነደሚጠቁሙት ለልጆች የቤት-ዕቃን በማዘጋጀት ውስጥ ሶስት መመዘኛዎች መታሰብ አለባቸው፡፡

 1. ቦታው በልጁ ላይ ሳይሆን ልጁ በቦታው የበላይነት እንዲኖረው የሚያደርግ ቦታ መመረጥ አለበት
 2. ልጆችን ለእንቅስቃሴ የሚያበረታታና የትኛውንም መጠንና አይነት ያለው፤ በተለይም ለትምህርታዊ እንቅስቃሴ የሚሆን ቡድን ለመመስረት የሚያስችል መሆን አለበት
 3. ምቾት፣ውበት እና መነቃቃትን መስጠት አለበት

እንደዚህ አይነት አካባቢን መፍጠር ለልጆች ፍቱን(ውጤታማ) የቤት-ዕቃዎች ስብስብ መፍጠር ብቻ ሳይሆን ለመኝታቤት አግባብነት ያለውና የተሟላ የቤት-ዕቃ ምርጫ ለማድረግ የሚያስችል ነው፡፡ በተለይም ልጆች ትምህርት-ቤት ከመግባታቸው በፊት ያለው ጊዜ ላይ ለእነዚህ ጉዳዮች ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል፡፡

የልጆች መኝታ-ቤት የቤት-ዕቃዎች አይነት

የመኝታ-ቤት ዕቃዎች በመኝታቤቱ አካባቢ የሚከናወኑ ክንውኖች የሚደረጉበትን ስፍራ  የሚያጠቃልሉ ናቸው፡፡ እነዚህም ክንውኖች መተኛት፣መጫወትና ራስን ማስተካከል በሚል ቀደም ብለው የተጠቀሱ ናቸው፡፡ ከዚህ በታች የእነዚህ ክንውኖች ማከናወኛዎች አልጋ፣የስራ ሰሌዳ፣የመቀመጫ ስፍራ፣የማከማቻና የማሳያ ስፍራ ብለን እያንዳንዳቸውን እናያለን፡፡

አልጋዎች

ልጆች በመተኛት ብዙ ጊዜ ያሳልፋሉ፡፡ ስለዚህ ደህንነቱ የተጠበቀ፣እያደገ ያለ አካላቸውን በጤናማ ሁኔታ የሚደግፍ ምቹ የመተኛ ስፍራ መስጠት አስፈላጊ ነው፡፡ ለአንድ ልጅ አልጋ ከማንቀላፊያ ስፍራነት የበለጠ ትርጉም ያለው መሆኑንም ማስታወስ ያስፈልጋል፡፡ ህፃናት የመንቃሳቀስ ችሎታቸውን የሚያዳብሩበት፤ ታዳጊ ልጆችም የታመቀ ሀይላቸውን የሚጠቀሙበት የሰውነት እንቅስቃሴ ማድረጊያም ነው፡፡ አለፍ ሲልም የመዝናኛ፣የማንበቢያ እና ከጓደኞች ጋር መሰባሰቢያም ነው፡፡በ1990 ሮበርትሰን የተባለው የዘርፉ አዋቂ የአልጋዎችን አይነት እንደየልጆቹ እድሜ የህፃናት አልጋ፣መካከለኛ አልጋ እና የአዋቂ ልክ አልጋ የሚል ስያሜ ሰጥቷቸዋል፡፡

የጨቅላ ህፃናት አልጋ

ይህን የአልጋ አይነት በመንደፍ ውስጥ ለደህንነት ሰፋ ያለ የማሰቢያ ጊዜ ተሰጥቶት መሆን አለበት፡፡ የህፃናት አልጋ ቅርጫትና ከፍታ ያለው የጎን ሽፋን አለው፡፡ በተለይም ቅርጫቱ ለመጀመሪያዎቹ ሁለት ወይም ሶስት ወራት የሚያገለግል ነው፡፡ የጎን ሽፋኖቹ አልጋው በሚወዛወዘወበት ጊዜ ህፃኑን በአስተማማኝ ሁኔታ ደህንነቱ እንዲጠበቅ የሚያደርግ ከፍታ ሊኖራቸው ያስፈልጋል፡፡ ለጥንቃቄ ሲባል የመሽከርከሪያው ድጋፎች አነስተኛ ኩርባነት እንዲኖራቸው ይደረጋል፤ የተረጋጋ እንቅስቃሴም ይኖራቸዋል፡፡ ተንጠልጣይ የህፃናት አልጋ ጠንካራ መሰረት፣ከብረት የተሰራ ጠንካራ የመሽከርከሪያ ነጥብ እና አልጋው እንዳይወዛወዝ በሚያደርግ አቀማመጥ ውስጥ ቆልፎ ለማቆየት የሚያስችል ንድፍ ያስፈልገዋል፡፡ የማይነቃነቅ መሰረት በህፃናት አልጋ ላይ ከሚያስፈልጉት አንዱ ነው፡፡

የህፃናት አልጋ በሁለት ዋና መጠኖች ይገኛሉ፡፡ እነዚህም የአውሮፓው (123ሳሜ በ60 ሳሜ) እና የአሜሪካው (144ሳሜ በ76ሳሜ) ናቸው፡፡ የአሜሪካዎቹ ጎናቸው ሊወሰድና በአልጋ መሸፈኛ ሊተካ የሚችል በመሆኑ ለብዙ ጊዜ መቆየት ይችላሉ፡፡ የአልጋው ጎኖች በቀጫጭን እንጨቶች፣ብርሀን አስተላላፊ ቴርሞ ፕላስቲክ ወይም በጨርቅ ወንፊቶች ሊሰሩ ይችላሉ፡፡ ይህም ህፃኑን በቀላሉ በአልጋው ውስጥ ለማየት ይጠቅማል፡፡

አይ ኤስ ኦ እና የአውሮፓ መስፈርት የአልጋው የማእዘን ቋሚዎች ከመደገፊያው የ15 ሚ.ሜ ወይም ከዛ በታች ከፍታ እንዲኖረው ወስነዋል፡፡ ይህም የህፃኑ ልብስ ተንጠልጥሎበት እንዳይቀር ነው፡፡ ምንም ቋሚ ዘንግ መጉደል የለበትም ዘንጎቹ ከ6ሳሜ ማለትም አራት ጣቶች በአንድ ላይ ከሚሰጡት ስፋት በላይ መራራቅ የለባቸውም፡፡ የነዚህ መስፈርቶች መሟላት የህፃኑ ጭንቅላት በመካከላቸው እናዳይቀረቀር ያደርጋል፡፡ የልጆች መጠለፍ አደጋን ለማስቀረት ሲባል በግርጌ የላይኛው ክፍል ላይ ቆርጦ በማውጣት የሚሰሩ መያዣዎች ወይም ጌጦች መኖር የለባቸውም፡፡ በሁለቱም የአልጋው መውረጃ ጎኖች፤ ለእያንዳንዳቸው አንድ መቆለፊያ መኖር አለበት፡፡ የአቆላለፍ ዘዴውና ተንቀሳቃሽ አካላቱ አስተማማኝ እና ህፃኑ የማይደርስባቸው መሆን አለባቸው፡፡

አንዳንድ የህፃናት አልጋዎች የተለየ ለፍራሽ ማሳረፊያ የሚሆን ከፍታ አላቸው፤ፍራሹን ዝቅ ለማድረግ የሚጠቀሙበት ዘዴ ሊለያይ ይችላል፡፡

ሌሎቹ ሶስት ወይም አራት እርከን ሲኖራቸው የህፃናት አልጋ ሁለት እርከን አለው፡፡ የህፃናት አልጋ ማንቀሳቀሻ(መፈንቅል) በቀላሉ መንቀሳቀስ ይችላል፡፡ ይህ ባይሆን ግን መፍታት፣ የታችኛው መደገፊያውን ማንቀሳቀስ እና መልሶ ማሰር ግድ ይሆናል፡፡ እነዚህ የከፍታ ልኬት አማራጮች በፍራሽ እና በጎኖች ከፍታ በማወቅ ህፃኑ ከአልጋው ዙሪያ ዘሎ የመውጣት ሙከራውን ለማደናቀፍ (ተስፋ ለማስቆረጥ) ይጠቅማሉ፡፡

ህፃኑ እራሱን ችሎ ከጎጆ አልጋው ውስጥ መውጣት ሲችል የአልጋው ሁኔታም አብሮት ይለወጣል፡፡ በአንዳንድ ሞዴሎች፤ ለመቀመጫነትም እንዲያገለግል ሲባል አንደኛው የጎን ክፍል ብቻ ይነሳል ወይም ሁለቱንም ጎኖቹን በማንሳት መካከለኛ አልጋ በማድረግ ለጥቅም ይውላል፡፡ በሌሎች ሞዴሎች ሁለቱም ጎኖቹን ማስወገድና ፍራሽ ማስረዘሚያን በመጠቀም የመኝታ ቦታው እንዲረዘም ይደረጋል፡፡ ማስረዘሚያው የመሳቢያ ቦታዎች ይዘውት የነበረውን ቦታ ይይዛል፡፡

መካከለኛ አልጋዎች

እነዚህ አልጋዎች እድሚያቸው ከሁለት እስከ አምስት አመት ሆኗቸው መራመድ ለጀመሩ (ድክድክ ለሚሉ) ህፃናት የሚሆኑ ናቸው፡፡ ከህፃናት አልጋነት ወደ መካከለኛ አልጋነት በመለወጥ ከሚገኙት በተጨማሪ ራሳቸውን ችለው በብቸኝነት የሚነደፉ ብዙ አይነት መካከለኛ አልጋዎች አሉ፡፡ ከህፃናት አልጋና ከአዋቂዎች አልጋ በተለየ መልኩ የተወሰነ የልኬት መጠን ደንብ የላቸውም፡፡ አንዳንድ መካከለኛ አልጋዎች እውነኛ ባልሆኑ(የጌጥ) አልጋዎች ዘይቤ ሲገኙ ሌሎቹ እጅግ ጥቃቅን የአዋቂ አልጋ አይነቶች ሆነው ይገኛሉ፡፡ ፍራሹ በቀጥታ በቀጫጭን እንጨት ላይ ይቀመጣል፤ መደገፊያም ሊኖረው ይችላል፡፡

Pin It on Pinterest

Share This