ከእንጨት የተሰሩ የቤተ-ዕቃዎች

ከሞላጎደል የትኛውም የእንጨት አይነት የቤት-ዕቃን ለመስራት ያገለግላል፤ግን አንዳንድ እንጨቶች በውበታቸው፣በዘላቂነታቸውና ለስራ ቀላል መሆናቸው ከሌሎቹ ይበልጥ እንዲወደዱ አድርጓቸዋል። ከ1900 በፊት አብዛኞቹን የቤት-ዕቃዎች እንደ ሉጥና ዋል-ነት ባሉ እንጨቶች መስራትና ብርቅ በሆኑ እንጨቶች መሸፈንና መለበጥ የተለመደ ነበር። ለቤት-ዕቃ መስሪያነት የሚያስፈልጉት የእንጨት አይነቶች በቀላሉ ያለችግር ይገኙ ስለነበር ማራኪነትና ዘላቂነት የጎደላቸው የእንጨት አይነቶች ድብቅ በሆኑ የቤት-ዕቃው ቦታዎች ላይ ብቻ ጥቅም ላይ ይውሉ ነበር። በዚህ ምክንያት ቅድመ-1900 የቤት-ዕቃዎች መልሶ ለመደነቅ የሚገባቸው ናቸው ቢባል ማጋነን አይሆንም።

እነዚህ ተመራጭ እንጨቶች ቁጥራቸው እየተመናመነ ዋጋቸውም እየጨመረ ሲመጣ የቤት-ዕቃዎች በስፋት በሚገኙ እንጨቶች ተሰሩ። በአሁኑ ጊዜ አብዛኞቹ የቤት-ዕቃዎች እንደ ጥድና ሙጫ ዛፍ ባሉ እንጨቶች እየተሰሩ ይገኛሉ። የቤት-ዕቃዎች የተሰሩበትን የእንጨት አይነት መለየት መቻል ሊያወጡ የሚችሉትን ትክክለኛ ዋጋ ለማወቅ ያስችላል።

ከጠንካራ እንጨት የተሰሩ የቤት-ዕቃዎች ከደማቅ ቡኒ እስከ ስስ ቡኒ ከዛም አልፎ የጠቆረ መልክ ሊኖረቸው ይችላል። ይህም ተፈጥሯዊ ሲሆን የሚከሰተውም በእንጨቱ ውስጥ ባለው የማዕድናት ስብጥር ምክንያት ነው። ይህ ተፈጥሯዊ ባህሪያቸው ከእንጨት የተሰሩ የቤት-ዕቃዎችን ማራኪ ገፅታ ያላብሳቸዋል፤በስፋት ጥቅም ላይ ለመዋላቸውም ምክንያት ነው ማለት ይቻላል።

አንዳንድ ጊዜ የቤት-እቃዎች በክፍሎቻቸው ማለትም በበርና መሳቢያቸው ወይም በሙሉ አካላቸው ላይ የተለያየ አይነት መልክ ሊያሳዩ ይችላሉ። ይህን ስንል ደግሞ ለምሳሌ በቁም-ሳጥንና ጠረጴዛ መሀከል የመልክ ልዩነት ይታይባቸዋል። ይህም የሚከሰው ስሪታቸው ከእንጨት በመሆኑ፣እንጨት ደግሞ በባህሪው በአየር ሁኔታና ጠባይ፣በነፍሳት (ተባይ)፣በወፎች፣በአፈር አይነቶች መደበላለቅና በአበቃቀሉ ሁኔታ የሚጠቃ በመሆኑ ነው።

የነዚህ የቤት-ዕቃዎች እድሜ እየጨመረ ሲሄድ የቀለም ባህሪያቸውና ድምቀታቸው እየተለወጠ ይሄዳል። የነዚህ ለውጦች መጠንና አይነት በተለያዩ ምክንያቶች ላይ ይመሠረታል። ይህም በእንጨቱ አይነት፣በቀለማቸውና በቀጥታ የሚያገኛቸው የፀሀይ ብርሀን መጠን ላይ ይወሰናል። በተጨማሪም ለጭስ፣ለኬሚካሎች ምናልባትም በረጅም ጊዜ ውስጥ ለሰውሰራሽ ብርሀን ያላቸው ተጋላጭነት የበራቸው ቀዳሚ የቀለም ለዛና ድምቀት እንዲለውጥ ያደርጋል። ይህ የቀለም ሁኔታ ለውጥ በየቀኑ እንቅስቃሴ ውስጥ ሊታይ ባይችልም በረጅም ጊዜ ሂደት ውስጥ ለዕይታ መውጣቱ አይቀሬ ነው። በዚህ ምክንያት ነው ቀድመው የነበሩ የቤት-ዕቃዎች ከአዳዲስ የቤት-ዕቃዎች ጋር ለመግጠም የማይችሉት። በተመሳሳይ ምክንያት የቀለም ናሙናዎችና በመሸጫ ቤቶች ያሉ ማሳያዎች የቤት-ዕቃዎቹ አገልግሎት በሚሰጡበት ጊዜ የሚኖራቸውን ገፅታ ወክለው ማሳየት አይችሉም።

ከእንጨት የተሰሩ የቤተ-ዕቃዎች ጥቅም

ጥንካሬና ዘላቂነት

ከእንጨት የተሰሩ የቤተ-ዕቃዎች ቶሎ ከጉዳት የሚያገግሙና በቀላሉ የሚጠገኑ ናቸው። ተፈጥሯዊና በማብሰያ ቤቶች ወይም በመመገቢያ ቤት ውሰጥ በመጫጫር የሚደርሱ ተደጋጋሚ ጉዳቶችን መቋቋም የሚችሉ ናቸው። ትንሽ ጥንቃቄ ቢደረግላቸው ከትውልድ ትውልድ መተላለፍ ይችላሉ።

ጉዳትን በቀላሉ አስቀድሞ መከላከል መቻል

ጥገና በሚያስፈልጋቸው ጊዜ ብዙ በማያደክም ሁኔታ ጥገናውን ማከናወን ይቻላል። እንዲሁ ለእንጨት ማፅጃነት በተዘጋጁ ማፅጃዎች ገፃቻውን ሁልጊዜ በአግባቡ በመጥረግ ከአቧራና ውሀ የሚደርስ ጉዳትን መቀነስ ይቻላል።

መሰረታዊ የቤት ማስዋቢያነት

ከእንጨት የተሰራ የቤት-ዕቃን በክፍል ውስጥ መጨመር ክፍሉ የሚሰጠውን ዕይታና ስሜት ይለውጣል። በየትኛውም አይነት ክፍል ውስጥ ግርማ ሞገስ፣ለዛና ውበት ያለው ውስብስብነት የመፍጠር ትልቅ አቅም አላቸው።  

ዋጋ 

ምንም እንኳን ከእንጨት የተሰራ የቤት-ዕቃን ለማግኘት ወጪ የሚያስወጣ ቢሆንም በቤተ-ዕቃ ማምረት ኢንዱስትሪው ውስጥ ካሉ በሌላ ቁስ ከተሰሩ የቤት-ዕቃዎች የበለጠ ዋጋ ያላቸው ናቸው። የተፈጥሮ ገፅታቸው በትክክል ስለማይመሳሰል እያንዳንዱ የቤተ-ዕቃ በራሱ መንገድ ልዩ ነው። በተመደበው ገንዘብ ልክ ጥሩ ገፅታ ያለው የቤት-ዕቃ ማግኘት ይቻላል። ለምሳሌ ከጥድ የተሰራ የቤት-ዕቃ ጥሩ ገፅታ ያለው በመሆኑና በጥንካሬውና በብዛት በመገኘቱም በቀላል ዋጋ የታወቀ ነው። ብርቅ በሆነው የሉጥ ዛፍ እንጨት የተሰራ የቤት-ዕቃ በዋጋው ውድነትና በውበትና ግርማሞገሱ የታወቀ ነው።

ለመጠቀም እንዲስማማ በሚያደርግ መልኩ ለመለዋወጥ መቻል

የነዚህ የቤት-ዕቃዎች ውበታቸው አንድም በጊዜ ውስጥ በመለዋወጥ ሁለተኛ፣ሶስተኛ ወይም አራተኛ አይነት ለማገኘት መቻሉ ነው። በማለስለስ፣በማቅለም ወይም በመቀባት ከእንጨት ለተሰራ የቤት-ዕቃ ሙሉበሙሉ አዲስ መልክ መስጠት ይቻላል።

የብረታ ብረት የቤት-ዕቃዎች

የጀርመን የንድፍ ጥበብን በመከተል የሚታወቀው ማርሴል ብሩወር በብስክሌት ስሪት ላይ ባየው ቅለትና ጥንካሬ በመማረክ ከክፍት አረብብረት የቤት-ዕቃዎችን በመስራት በ1925ዓ.ም እንደጀመራቸው ይገመታል። በዘመኑ ከነበሩት የቤት-ዕቃዎችም መካከልም ታዋቂነትን ለማግኘት ጊዜ አልፈጀባቸውም።

ዋናው የሚሰሩበት ጥሬ ዕቃ ብረት የሆኑ የቤት-ዕቃዎች ናቸው። የተለያዩ የብረት አይነቶችን በመጠቀም ይሰራሉ። ከነዚህም ክውር ብረት፣የማይዝግ አረብ ብረት፣የካርበን ብረትና አሉሚንየም እንደ ምሳሌ የሚጠቀሱ ሲሆኑ ከቢሮ እስከ ቤት ድረስ ላሉ ቦታዎች የሚያገለግሉ ናቸው።

ከክውር ብረት የሚሰሩ የቤት-ዕቃዎች

በጥንካሬ፣ክብደት፣ጥብቅ ስሪታቸውና ፅኑነታቸው ከቤት-ውጪ ለመጠቀም ይመረጣሉ። ዋነኛ እንደ ጉዳት ሊታይ የሚችል ባህሪው በእርጥበታማ አየር ውስጥ በቀላሉ ለዝገት ተጋላጭ መሆኑ ነው። ለዚህም መንስዔው ከሁሉም የብረት አይነቶች በተለየ ቅልቅል የሌለው ንፁህ የብረት አይነት ስለሆነ ነው።

ከማይዝግ የአረብብረት የሚሰሩ የቤት-ዕቃዎች

ዘመናዊ የመኖሪያ ቤት የቤት-ዕቃዎች በአብዛኛው ከዚህ የብረት አይነት ይሰራሉ። በቤት-ዕቃዎች ውስጥ ብዙዎቹ ማጠፊያዎች፣ማንሸራተቻዎች፣ድጋፎችና አጠቃላይ ዙሪያ አካላት ከማይዘግ አረብብረት የተቀናበሩ ናቸው። ከፍ ያለ ወጥነታዊ ብርታት ስላላቸው በአብዛኛው ውስጣቸው ክፍት የሆኑና አነስተኛ ክብደት የሚሸከሙ የቤት-ዕቃዎች ከዚህ የብረት አይነት ሲሰሩ ተመራጭነት አላቸው። ለተጠቃሚም ቢሆን በቀላሉ ተደራሽነት አላቸው።

ከአሉሚንየም የሚሰሩ የቤት-ዕቃዎች

በቀላል ክብደትና ዝገትን በመከላከል አቅማቸው ተለይተው ይታወቃሉ። የተለያየ ቅርፅና ህትመት የሚኖራቸው የቤት-ዕቃዎች በተለይም ለየት ያለ ዕይታ የሚፈጥሩ ወንበሮች የዚህ ዋነኛ ምሳሌ ተደርገው ይጠቀሳሉ። እነዚህ የቤት-ዕቃዎች ከዝገት ነፃ የሚሆኑበት ምክነያት በዙሪያቸው ያሉት የአሉሚንየም አቶሞች አሊሚንየም ኦክሳይድ የተባለ ውህድ ፈጥረው ስለሚቀመጡ ነው።

ዋነኛው በብረት የተሰሩ የቤት-ዕቃዎች ጥቅም ዘላቂነታቸው ነው። ለምሳሌ አብዛኞቹ ብረት አልባ የቤት-ዕቃዎች በክረምት ወራት ውጪ ቆይተው ከነበራቸው ውበት ጋር ወደ ፀደይ ወራት መሻገር አይችሉም። ተገቢ በሆነው የጥንቃቄ መንገድ ከተያዙ እስከ 30 አመት ማገልገል ይችላሉ። ሙቀት መቋቋም መቻላቸውና የዝገት መከላከያን አንድ ጊዜ በመጠቀም ከመበስበስ መጠበቅ መቻሉ እድሳት የሚያስቀር ጥሩ ባህርያቸው ነው።

ከብረት የሚሰሩ የቤት-ዕቃዎች የሚሰጧቸው ጥቅሞች

ደህንነት

ስሪታቸው ከብረት የሆኑ የቤት-ዕቃዎች እሳት የመቋቋም፣ውሀን የመቋቋም እና ከስርቆትም እራሳቸውን የመጠበቅ አቅም ስላላቸው በደህንነታቸው እነዲታወቁ ሆኗል። ይህ ባህሪያቸው ምቹ ባልሆኑ ቦታዎችና ልዩ ለሆኑ እቅዶች ተመራጭ እንዲሆኑ አስችላቸዋል። የማይጠበቁ ችግሮችን አነስተኛ በሆነ ወጪ ለመፍታትም የተሻለ እድል የሚሰጡ የቤት-ዕቃዎች ናቸው። ከአገልግሎታቸው ጋር ተመጣጣኝ በሆነ ውፍረት ከተዘጋጁና መገጣጠሚያዎቻቸው በአግባቡ ከተሰሩ፤አደጋ የመድረሱንና ጥገና የማስፈለጉን እድል እጅግ አናሳ ያደርጋል።

ጥሩ የሆነ የቦታ አጠቃቀም

ከሌሎች ቁስ አካላት ከተሰሩ የቤተ-ዕቃ አይነቶች አንፃር ጥሩ ስለሆኑ በክፍል ውስጥ ያለውን ቦታ በሚገባው መንገድ ለመጠቀም ያግዛሉ።በአሁኑ ጊዜ በህንፃዎች ላይ ያለው የቢሮ-ኪራይ ዋጋ ውድነት እየጨመረ ይገኛል። በመሆኑም አነዚህ የቤት-ዕቃዎች ይህን ሁኔታ በማሻሻል ላይ ያላቸው ሚና ለመገመት የሚከብድ አይደለም። ተፈላጊነታቸውና ታዋቂነታቸው እየጨመረ የመጣበት ምክንያትም እነዚህን ጥቅም በመስጠታቸው ነው።    

ጤናማነት

ከብረት የተሰሩ የቤት-ዕቃዎች በሚመረቱበት ጊዜ ጥቅም ላይ የሚውሉት ላሜራዎች ብቻ በመሆናቸው ለመጣበቅ ብየዳን እንጂ ሙጫ ወይም መሰል ኬሚካሎችን አይፈልጉም። ጎጂ ቁሶችንም ይዘው ወደ ሰዎች ኑሮ ውስጥ አለመግባታቸው ከስዎች ጤና ጥበቃ አንፃር ጠቃሚነታቸው እንዲጎላ አድርጓል።

ከአካባቢ ጋር ያላቸው ተስማሚነት

በአሁኑ ጊዜ የሰዎች ስሜት እጅግ ተለዋዋጭነት ያለው ሆኗል። አንድ ዕቃ አገልግሎት የመስጠት አቅም ቢኖረው እንኳን በመልኩ ሳቢነት ደካማነት ብቻ ከግምት በማስገባት የአገልግሎት ዘመኑ ከአምስት አመት ያነሰ እንዲሆን ይደረጋል። በዚህም ምክንያት በምድራችን ላይ ማዕድናት እየተመናመኑ፤ በምትኩ ቆሻሻ(ትርኪ ምርኪ) እየተከማቸ ይገኛል።ከብረት የተሰሩ የቤት-ዕቃዎችን በብዛት መጠቀም የቤት-ዕቃዎቹ ከተወገዱ በኃላ መልሶ መጠቀም መቻሉና በእሳትም ሆነ በተፈጥሯዊ አበስባሾች በቀላሉ ወደ አፈርነት መለወጥ መቻላቸው ከአካባቢ ጋር ተስማሚ ስለሚያደርግ እንደ ትልቅ ጥቅምም ሊታይ የሚገባ ነው።

ጠንካራ የመቋቋም ችሎታ

ብረት በተፈጥሮው ውጥረትን የመቋቋም ችሎታ አለው። ስለዚህ ከብረት የተሰሩ የቤት-ዕቃዎችም እንዲሁ ከፍተኛ ውጥረትን የመቋቋም ችሎታ አላቸው። በዙሪያችን ያሉ የብረት ቁምሳጥኖች፣ባለመሳቢያ መደርደሪያዎችና ሳጥኖች ከሚሸከሙት ክብደት ጋር በተመጣጠነ የብረት መጠን ይሰራሉ። ይህ የአሰራር ሁኔታ ንድፍ አውጪዎች ወይም ገንቢዎች መጠቀም ያለባቸው የብረት ውፍረት መጠን በአጋጣሚ ካልተዛባ በስተቀር ከብረት መሰራታቸው ውጥረት የመቋቋም ችሎታቸውን አስተማማኝ ደረጃ ላይ የሚያደርሰው መሆኑን ያመለክታል። በተጨማሪም በበሮቻቸው ላይ ያለው ማጥበቂያና በመደርሪያዎቻቸው ላይ ያለው ማጠንከሪያ ተጨማሪ ክብደትንና ውጥረትን እንዲቋቋሙ ከሚረዳቸው ምክንያት ውስጥ ሊጠቀስ የሚችል ነው።

ስፋት ያለው ተግባርን ማከናወን

እነዚህ የቤት-ዕቃዎች በትምህርት ቤቶች፣በቢሮዎች፣በፋብሪካዎች፣በመልበሻ ክፍሎች፣በግምጃ ቤቶች፣በመንግስት መስሪያቤቶች፣በስፖርት ማዘውተሪያዎች፣በሸቀጣ ሸቀጥ መሸጫ ሱቆች፣በሰራተኛ ማረፊያ ቤቶችና በመሳሰሉ ብዙ አገልግሎት ሰጪና አምራች ተቋማት ውስጥ አገልግሎት ይሰጣሉ።

Pin It on Pinterest

Share This