ጅማሮ፦

የጥንት ዘመን ስልጣኔን ስናነሳ ግብፅን አለማንሳት ከባድ ነው በዚያ ዘመን ስልጡን ሀገሮች  ተብለው ይጠቀሱ ከነበሩ ከኢትዮጵያ፣ፋርስ፣ህንድ እና ቻይና  ጋር የምትመደብ ሀገር ነበረች። ታዲያ ይህ የግብፅ ስልጣኔ ዕደጥበብ( ጌጣጌጥ)፣ኪነ ህንፃ እና ቤት የማስዋብ ጥበብ(Interior Design)  ላይ የራሱ የሆነ አስተዋፅኦ ሊያሳርፍ ችሏል፡፡ በዚህ ብቻ ሳይገታም ዛሬ ድረስ ባለው  የምዕራባውያን አንዳንድ ሥነ-ጥበብ ዘይቤ ላይ  አሻራው ያታያል፤ ለአብነት ያህል በይበልጥም በአሥራ ዘጠነኛው ክፍለዘመን መጀመሪያ ላይ ይህ የጥንት ግብፃውያን  ጥበብ የተለያዩ ዘመዊ ማሻሻያዎች ተደርገውለት በተለያዩ የጌጣጌጥ ቁሳቁሶች ላይ እንዲሁም የፈርኒቸር መገልገያዎች ላይ  ይታይ ነበር፡፡የጥንታዊቷ ግብፅ ጥበብ ቅንዓት  ናፖሊዮን ግብፅን እንዲወር አድረጎታል፡፡

የጥንት ግብፃውያንን የስነ ጥበብ ስራዎችን ይሰበስብ የነበረው ቶማስ የተባለ ባለሀብት ዱቼስ በሚባል  ጎዳና ላይ  በሚገኘው  የግል ክፍሉ ውስጥ  የግብፃዊያንን ጥንታዊ ቅርሶች ለማሳየት እነዚህን ስራዎች በአንድ ጋለሪ ውስጥ ከማስቀመጥ በተጨማሪ “የቤት ዕቃዎች እና የውስጥ ማስጌጫ”   በተባለው መጽሐፉ ላይ እነዚህን  ከፊል ስራዎች አውጥቶ ለማሳየት ሞክሮ ነበር፡፡ ታዲያ መጽሐፉ ይህ ባለሀብት በጥንት ግብፅውያን  የመቃብር ሥዕሎች ላይ ተስለው የሚገኙትን  የተለያዩ መገልገያዎችን( ወንበሮችን ፣ ጠረጴዛዎችን) እንዴት ይጠቀሟቸው እደነበር ከማሳየቱም በተጨማሪ ሌሎችም በዚህ በመሳብ በተሻሻሉ ሰራዎች ብቅ እንዲሉ አስችሏል፡፡ 

ኳድራቱራ 

 ይህ እንግሊዘኛ ቃል በ 17  ኛው ክፍለ ዘመን የተዋወቀ እና  በብዛት በባሮክ አርቲስቶች ዘንድ ተወዳጅ የሆነ  ስነጥበብን  የሚገልፅ ቃል ነው፡፡ ምንም እንኳን በሥነ-ሕንጻ እና በቤት ውበት አንፃር የግድግዳዎችን “መከፈት” ሊያመለክት ቢችልም ፣ ቃሉ አብዛኛውን ጊዜ ከጣሊያኖች የጣሪያ ሥዕል ጋር ይዛመዳል፡፡ ከሌሎች በተለየ መልኩ የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀምም ግልጋሎት ሊሰጡ የሚችሉ ለየት ያሉ የፈርኒቸር ዲዛይኖችንም አስተዋውቀዋል፡፡ ጥበባዊ አቀራረቦች ላይ ጥገኛ የሆኑት የተለያዩ የጣሪያ ጌጣጌጦች በቀጥታ በ 17 ኛው ክ/ዘመን ላይ በነበሩ ንድፈ ሀሳቦች ላይ በይበልጥም ከሕንፃ ቦታ አመራረጥ ጋርም የተሳሰረ በመሆኑ በአጠቃላይ አካታች ሊባል በሚችል መልኩ የሕንፃ ፣ የሥዕል እና የቤት ውበት ላይ ትኩረቱን ያደረገ ነበር፡፡ 

ሰዎች ከመጀመሪያው ስልጣኔ አንስቶ የተፈጥሮ ቁሳቁሶችን ማለትም እንደዛፍ ጉቶዎች እና ድንጋዮችየመሳሰሉትን እንደ ቤት እቃነት ይጠቀሙ ነበር ፡፡ በርካታ የአርኪዎሎጂ ጥናቶች ሰዎች የእንጨት፣የድንጋይ እና የእንስሳት አጥንቶችን በመጠቀም የተለያዩ የቤት ቁሳቁሶችን ከጥንት ጀምሮ መሥራትና መቅረጽ እንደጀመሩ ያሳያሉ፡፡  ለምሳሌ ያህል በሩሲያ  በአንድ ዙፋን ላይ ተቀምጣ የምትታየው የአንዲት እንስት ቅርፅ፣የተለያዩ ከድንጋይ የተቀረፁ ማስቀመጫዎች  እና አልጋዎች ይጠቀሳሉ፡፡ እንደ መገጣጠሚያ ያሉ ውስብስብ የግንባታ ቴክኒኮች  በጥንታዊ ግብፅ  የመጀመሪያ ሥርወ-መንግሥት ዘመን ተጀምረው የነበረ ሲሆን  በዚህ ዘመን በርጩማዎችን እና ጠረጴዛዎችን ጨምሮ አንዳንድ ውድ በሆኑ ብረቶች እና በዝሆን ጥርስ ተጊጠው  የተገነቡ  ቁሳቁሶችም ተጠቃሽ ናቸው ፡፡ይህ  የቤት ቁሳቁሶች ዲዛይን የእድገት ሂደት ለውጥ  በጥንታዊ ግሪክ  እና  ሮም  ስልጣኔ ውስጥ አንፃራዊ መሻሻል አሳይቷል ፣ በዚህ ዘመን በተለያዩ ዲዛይን የተሰሩ አልጋዎች እና ዙፋኖች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ወደ መካከለኛው ዘመን ስንሻገር በአሥራ አራተኛው እና በአሥራ አምስተኛው ክፍለ ዘመን   በጣሊያን  ህዳሴ  ወቅት የቤት ዕቃዎች ዲዛይን የተስፋፋ ሲሆን አብዛኛውን ጊዜም በጌጣጌጥ ያጌጡ ነበሩ፡፡  በደቡባዊም ሆነ በሰሜን አውሮፓ በአስራ ሰባተኛው ክፍለ ዘመን  ንድፈሀሳቦቹ የተሻሻሉ ሲሆን የኳድራቱራ ፅንሰ ሀሳብም በስፋት የተተገበረ ሲሆን በአሥራ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመንም የበለጠ ተሻሽሎ እና ለቀጣዩ ዘመንም መሰረት ተጥሎ የታለፈበት ጊዜ ነበር፡፡በነዚህ በተጠቀሱት ዘመናት ጥቅም ላይ የዋሉ እፅዋት፣ማእድናት ሲሆኑ በብዛት ሊባል በሚችል መልኩ  ጥቅም ላይ የዋሉት ግን የእዋት ዝርያዎች ሲሆኑ አብዛኛውን ጊዜም ጥራት ያላቸው የቤት ዕቃዎች የሚሠሩት ከዋንዛ ፣ከፅድ፣ ከኦክ፣ ከሜፕል ፣ ከማሆጋኒ ፣ ከዋልኖት  እና ከቼሪ እንጨቶች ነበሩ፡፡

 ወንበሮች

ወንበር በጣም ጥንታዊ  እና ከሚታወቁ የቤት ዕቃዎች መካከል ሲሆን ኢንሳይክሎፔዲያ ብሪታኒካን ጨምሮ ፀሀፊዎች  በጣም አስፈላጊ እንደሆነ አድርገው ይመለከቱታል ፡፡  ከተግባራዊ ዲዛይን በተጨማሪ ፣ መቀመጫዎች ከጥንት ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ  በተለያዩ አስፈላጊ ጌጣጌጦች  ተጊጠው አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ ፡፡ ይህ እንደ ስነ-ጥበባት ሥራ የታሰቡ  እና  በተለያዩ ዲዛይን የተሰሩት እንዲሁም የማህበረሰብን እሴት የሚያሳዩት ወንበሮችን በብዛት መጠቀም ከነባራዊ አገልግሎታቸው በተጨማሪ  ቃጫ፣ ቆዳ ፣ ዳንቴል የመሳሰሉትን ሲያካትቱ ደግሞ ስነጥበብንም በማጉላት ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ይሆናል ፡፡

   ሶፋዎች                        

የጥንት ዘመን ሶፋዎች ግሩም እና ድንቅ ናቸው አስገራሚ የሆኑ ግብአት በመጠቀም ይሰራሉ ፣ሶፋዎቹም ውድ ከመሆናቸው የተነሳ አብዛኛዉን ግዜ የሚገኙት የነገስታት፣የመኩዋንንት አና ባለስልጣናት እንዲሁም በባላሃብቶች ቤት ውስጥ ነበር። ሶፋዎቹ ለመሰራት የተለያዩ  ድንቅ የሆኑ ቁሳቁሶችን ይጠቀማሉ ለምሳሌ ዋንዛ፣ግራር፣ቀርካ፣ከማሆጋኒ ፣ ዋልኖት ፣ ወዘተ..ተጠቃሽ ሲሆኑ በተጨማሪም የነብር ቆዳ፣ የአንበሳ ቆዳ እና ሌሎችም ለሶፋዎቹ ተጨማሪ ውበት ለማጎናፀፍ ጥቅም ላይ ውለዋል።በጥንቱ ዘመን  ንገስታቱ በፍርድ ሸንጎ ላይ ሲሰየሙ  የሚጠቀሙት እነዚህን  በተለያዩ ጌጣጌጦች ያጌጡ ቁሳቁሶችን ነበር።

አልጋዎች

የጥንት ዘመን አልጋዎች  በጣም አስገራሚ የሆነ ውበት አላቸው አልጋዎቹም በተለያየ አይነት ዲዛይን ይሰራሉ።ለምሳሌ፦ ከእንጨት ፣ ከድንጋይ፣ ከጣውላ ፣ ከብረት ፣ ከቀርካ…ወዘተ በመፈልፈልም ይሰራሉ።

የልብስ ማስቀመጫዎች

    እንደ ዛሬ አለም በቴክኖሎጂ ከመዘመኑ በፊት ሰዎች ልብሶቻቸውን ለማስቀመጥ የተለያየ አይነት ዘዴ የሚጠቀሙ ሲሆን ለምሳሌ ፣ሳጥን፣ ቁም ሳጥን ፣የልብስ መደርደሪያዎች ..ወዘተ ተጠቃሽ ሲሆኑ እውቅ ባለሙያዎችም ለነገስታት በልዩ ዲዛይን የተለያዩ የልብስ ማስቀመጫዎችን በመስራት ግልጋሎት ሰጥተዋል። የማስቀመጫው የላይኛው ክፍልም በወርቅ ወይም በነሃስ ይለበጥ ነበር።

Pin It on Pinterest

Share This