የመመገቢያ ክፍሎች የቤተሰብ አባላት እንዲሁም ጓደኛሞች ጣፋጭ ምግቦችን የሚመገቡባቸው፣ወዳጅነትን የሚያጠነክሩባቸው፣ ውይይት የሚያደርጉባቸው  እና   ልዩ ጊዜን ለማሳለፍ የሚሰባሰቡባቸው ክፍሎች ሲሆኑ ከተራ የመመገቢያ ክፍልነት  እስከ በዓላት ግብዣዎች እንዲሁም ልዩ ስፍራ የሚሰጣቸው ቤተሰባዊ ሁነቶች የሚፈፀሙባቸው ክፍሎች በመሆናቸው፤ ሀሴት የሚደርጉባቸው እና ለረዥም ጊዜ የሚቆዩ ትዝታዎች የሚሸመቱባቸው ቦታዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ክፍሎች ከሚሰጡት ዘርፈብዙ ጠቀሜታ አንፃር  ለእነዚህ ክፍሎች ጥሩ ከባቢን እና ገፅታን መፍጠር ጊዜ ተወስዶ ሊታሰብበት የሚገባው  ቁልፍ ነገር ነው፡፡እነዚህ ክፍሎች  እንዲሰጡ ከሚፈለገው አገልግሎት በተጨማሪ  አስፈላጊውን ውበት እንዲላበሱ  ከታች የተዘረዘሩት ጠቃሚ ምክሮች ቢተገበሩ መልካም ነው፡፡

ጠረጴዛዎችን ማዘመን

የመመገቢያ ክፍል ዋና አካል እንደመሆኑ መጠን የመመገቢያ ክፍልን ጠረጴዛ በትክክል ማስጌጥ አስፈላጊ ነው ፡፡ለዚህም ተግባር ከእርሶ ዝንባሌ እና ከቤቶ ገፅታ ጋር የሚዛመድ የመመገቢያ ጠረጴዛ መምረጥ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ነው፤ለአብነት ያህል  የመመገቢያ ክፍሎ ባህላዊ ገፅታ የተላበሰ ከሆነ ባህላዊ የመመገቢያ ጠረጴዛዎችን ምርጫ ማድረጉ ለክፍሉ ተጨማሪ ግርማሞገስ ሲያላብሰው፤በአንፃሩ ቤቶ ዘመናዊ ገፅታ የተላበሰ ከሆነ ዘመኑ በሚጠይቀው ውበት እና  ጥራት የተሰሩ የመመገቢያ ጠረጴዛዎችን መምረጡ አስፈላጊ ይሆናል( ረዥም አራት ማእዘን እና ክብ ቅርፅ ያላቸውን   የመመገቢያ ጠረጴዛዎችን ሰፊ የመመገቢያ ክፍል ውስጥ መጠቀሙ የሚመረጥ ነው)፤ በተጨማሪም  በጠንካራ መስታወት የጠረጴዛውን የላይኛውን ክፍል ማስጌጥ ለመመገቢያ ጠረጴዛው የተለየ ውበት የሚያጎናፅፈው ሲሆን  ይህም ጥሩ ስሜት ለመፍጠር ይረዳል፡፡ከዚህ ጎን ለጎን የተለያዩ የመመገቢያ ክፍል ወንበሮችን መጨመርና የክፍሎን የማስተናገድ አቅምም ከግምት ማስገባት አስፈላጊውን የመመገቢያ ጠረጴዛ ለመምረጥ ይረዳዎታል፡፡

ክፍሉን በቁምሳጥን ማስዋብ

ማራኪ ቁም ሳጥኖችን ከተለያዩ መገልገያ ቁሳቁሶች ጋር ማቀናጀት  የመመገቢያ ክፍልን ገፅታ ለማሻሻል የሚረዳ ሲሆን በተለያየ አይነት ዲዛይን የተሰሩ የቁም ሳጥን አይነቶችን መጠቀም ከተለመደው አገልግሎታቸው ጎን ለጎን ተጨማሪ ውበትን በማላበስ  እይታን ለመሳብ ያገለግላል፡፡

የክፍሉን መብራት ማስዋብ

አብዛኛውን ጊዜ  የተለያዩ  የመኖሪያ ቤት ክፍሎችን ለማስዋብ የተለያዩ የመብራት ስብጥሮችን መጠቀሙ የሚመረጥ ሲሆን ለዚህም ተግባር በተለያየ አይነት፣ቅርፅ እና ዲዛይን የተሰሩ የመብራት አይነቶችን መጠቀም ተገቢ ሲሆን ይህም ክፍሉን ደማቅ እና ልዩ ለማድረግ አይነተኛ ሚና ይጫወታል፡፡

ክፍሉን በምንጣፍ ማስዋብ

የቤት ውበትን የሚጨምሩ በተለያየ አይነትና ዲዛይን የተሰሩ በርካታ የምንጣፍ አይነቶች ሲገኙ በተለያዩ ቀለማት ያሸበረቁት እነዚህ የምንጣፍ አይነቶች የቤትን ውበት በመጨመር ረገድ አይነተኛ ሚና ይጫወታሉ፤ስለዚህ ከክፍሉ አጠቃላይ ሁኔታ ጋር ሊዛመዱ የሚችሉ የምንጣፍ አይነቶችን መምረጥ አስፈላጊ ነው፡፡

የክፍሉን ግድግዳ ማስዋብ

የአንድን ክፍል ውበት በመጨመር ረገድ ጉልህ ሚና ከሚጫወቱት መካከል ግድግዳን ማስዋብ አንዱ ሲሆን ይህንንም የተለያዩ ቀለማትን፣ባህላዊ እና ዘመናዊ ጌጣጌጦችን በመጠቀም ማስዋብ ይቻላል ይህንንም በማድረግ  ክፍሉ ባህልን እና ቅርስን አጉልቶ እንዲያሳይ በማድረግ የክፍሉን ማራኪነት ማሳደግ ይቻላል፡፡

Pin It on Pinterest

Share This