መስታወት የአንድን ቦታ ድባብ ያሳድጋል፡፡ያለ ከፍተኛ በጀት  በቤትዎ ላይ ለውጥ ሊያመጣ የሚችል የቤት ማሻሻያ ካስፈለጎት መስታወቶችን እንደአማራጭ መጠቀም አስፈላጊ ሊሆን ይችላል፡፡የቤት ውበት ቁልፉ ነገር ያለው ጌጣጌጡ ላይ ሲሆን የቤትን ንድፍ የሚያወጡ ባለሙያዎች መስታወቶችን እንደጌጣጌጥ በመገልገል የክፍሉን ገፅታ ማሻሻል ይቻላል ይላሉ፡፡ መስታወት ለዘርፈብዙ አገልግሎት የሚውል ቁስ ነው:: ይህ ቁስ የሚዘጋጀው ከብርጭቆ ሲሆን ከማንኛውም ብርጭቆ የሚለየውም አንድን ክፍል ውብ፣ብሩህ፣እንዲሁም በጣም ሰፊ አድርጎ የማሳየት አቅም አለው፡፡ምንም እንኳን በገበያ ውስጥ ብዙ አይነት የመስታወት አይነቶች ቢኖሩም እርስዎ የሚያስቡትን ውበት እውን ለመድረግ  ምን ዓይነት ውበት ለመፍጠር እንደሚፈልጉ ቀድሞ ማስቡ አስፈላጊ ነው፡፡ ለዚህም በዋናነት ቦታ እና ትክክለኛውን የመስታወት መጠን መምረጥ ያስፈልጋል ፡፡

ቦታ

ለክፍሎ የሚሆን መስታወት ፍለጋ ከመጀመሮ በፊት መስታወቱ የሚቀመጥበትን ቦታ መምረጥ የመጀመሪያው እርምጃ መሆን አለበት፡፡ለእይታ ማራኪ የሆነ ቦታ መምረጥ እዲሁም  መስታወቱ  ለቦታው በተገቢው ቁመት ላይ መቀመጡንም ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ምንም እንኳን በየትኛውም ክፍል ውስጥ የማስቀመጥ ምርጫ ቢኖሮትም ከሚመርጡት ክፍል ውስጥም ቢሆን የትኛው ቦታ ላይ መቀመጥ እንዳለበት ጊዜ ተወስዶ መታሰብ አለበት ምክንያቱም እርሶ የሚያስቀምጡበት ቦታ ብርሀንን እንዲያንጸባረቅ ካለስቻለ ብዙም ፋይዳ አይኖረውም ምክንያቱም የመጨረሻው ግብ ብርሀንን በማንጸባረቅ ውበት ለመፍጠር መሆን አለበት፤ እንዲሁም ለግዢ ከመውጣቶ በፊት የሚያስቀምጡበትን ቦታ በፎቶግራፍ ፋይል ማድረጉ የትኛውን መስታወት ቢጠቀሙ የተሻለ እንደሆነ ይጠቁሞታል፡፡

ተስማሚውን መጠን መምረጥ

ለቤቶ የሚያስፈልገውን ተስማሚውን የመስታወት መጠን እና አይነት (ክብ፣ባለ አራት ማዕዘን፣ኮንኬቭ) ማወቅ ተገቢውን የመስታወት አይነት ለመምረጥ ቁልፍ መስፈርት ሲሆን ይህም የሚመሰረተው የሚያስቀምጡበትን የቦታ ስፋት ከግምት በማስገባት ይሆናል፡፡ምክንያቱም የሚመርጡት የመስታወት አይነትም በክፍሉ ገፅታ ላይ ተፅእኖ ማሳደሩ የማይቀር ስለሆነ ነው፡፡ቀጥሎ ከተዘረዘሩት የመስታወት አይነቶች ምርጫዎን ቢያደርጉ መልካም ነው::

ዝርግ መስታወት፡- እነዚህ ምስሎችን በመደበኛ መጠኖቻቸው የሚያንፀባርቁ ጠፍጣፋ መስተዋቶች ሲሆኑ በአብዛኛው በመኝታ ክፍሎች እና በመታጠቢያ ቤቶች ውስጥ የሚያገለግሉ በጣም የተለመዱ የመስታወት ዓይነቶች ናቸው፡፡

ኮንኬቭ መስታወት፡- እነዚህ የመስታወት አይነቶች ልክ እንደ ማንኪያ ወደ ውስጥ የሚዞሩ  ሉላዊ መስተዋቶች  ሲሆኑ  ከፍተኛ  ውበት የመፍጠር አቅም ስላላቸው ብዙ ጊዜ በሳሎን ውስጥ አገልግሎት እንዲሰጡ ይደረጋል፡፡

እስቴትመንት መስታወት(Statement mirrors)፡- እነዚህ የጌጣጌጥ መስታወቶች የመመገቢያ ክፍሎችን ለማስዋብ የሚረዱ ናቸው፡፡

አራት ማእዘን መስታወት፡- መጠናቸው አራት ማዕዘን የሆኑ መስታወቶች ክፈፍ ቢኖራቸው የሚመረጥ ሲሆን ክፈፍ ባይኖራቸውም እንኳን የክፍሉ አካል ሆነው በመታየት ወደተሰቀሉበት ቦታ ትኩረት የመሳብ አቅም አላቸው፡፡ወደጎን ከተቀመጡ ክፍሉን ሰፊ አድርጎ ማሳየት ሲችሉ በቁመታቸው ከተሰቀሉ ደግሞ ጣሪያውን ረዥም አድርጎ በማሳየት ለጣሪያው ተጨማሪ ውበት ይሰጣሉ፡፡

አነስተኛ/መካከለኛ መጠን ያላቸው መስታወቶች፡- እነዚህ የመስታወት አይነቶች መጠናቸው አነስተኛ ወይም መካከለኛ ስለሆነ  በቤት ውበት ላይ  ትልቅ ተጽእኖ የሚያሳድሩት በይበልጥ ከሌሎች የመስታወት አይነቶች ጋር ተደባልቀው ከተቀመጡ ነው፡፡ምክንያቱም እያንዳንዱ መስታወት ክፍሉን እና ብርሀኑን በተለየ መንገድ ማንፀባረቅ ስለሚችል ነው፡፡ ስለሆነም ጥሩ ቦታ ላይ መቀመጥ ቢችሉ የሚፈለገውን ውበት የመፍጠር አቅም ይኖራቸዋል፡፡

Pin It on Pinterest

Share This